Hosea 10

1እስራኤል የተንዠረገገ ወይን ነበር፤
ብዙ ፍሬም አፈራ፤
ፍሬው በበዛ መጠን፣
ብዙ መሠዊያዎችን ሠራ፤
ምድሩ በበለጸገ መጠን፣
የጣዖታት ማምለኪያ ዐምዶችን አስጌጠ።
2ልባቸው አታላይ ነው፤
ስለዚህም በደላቸውን ይሸከማሉ።
እግዚአብሔር መሠዊያዎቻቸውን ያወድማል፤
የጣዖት ማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ያፈራርሳል።

3እነርሱም፣ “እኛ ንጉሥ የለንም፤
እግዚአብሔርን አላከበርንምና፤
ንጉሥ ቢኖረንስ፣
ምን ሊያደርግልን ይችል ነበር?” ይላሉ።
4ከንቱ ተስፋ ይሰጣሉ፤
በሐሰት በመማል፣
ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፤
ስለዚህም ፍርድ፣
በዕርሻ ውስጥ እንደሚገኝ መርዛማ ዐረም ይበቅላል።
5በሰማርያ የሚኖረው ሕዝብ፣
በቤትአዌን ስላለው የጥጃ ጣዖት ይፈራል፤
ሕዝቡም ያለቅስለታል፤
በክብሩ እጅግ ደስ ያላቸው ሁሉ፣
አመንዝራ ካህናትም እንደዚሁ ያለቅሱለታል፤
በምርኮ ከእነርሱ ተወስዷልና።
6ለታላቁ ንጉሥ እንደ እጅ መንሻ፣
ወደ አሦር ይወሰዳል፤
ኤፍሬም ይዋረዳል፤
እስራኤልም ስለ ጣዖቱ ያፍራል።
ወይም ስለ ምክሩ

7ሰማርያና ንጉሧ፣
በውሃ ላይ እንዳለ ኵበት ተንሳፍፈው ይጠፋሉ።
8የእስራኤል ኀጢአት የሆነው፣
የአዌን ማምለኪያ ኰረብታ ይጠፋል፤
እሾኽና አሜኬላ ይበቅልባቸዋል፤
መሠዊያዎቻቸውንም ይወርሳል፤
በዚያን ጊዜ ተራሮችን፣ “ሸፍኑን!”
ኰረብታዎችንም፣ “ውደቁብን!” ይላሉ።
9“እስራኤል ሆይ፤ ከጊብዓ ጊዜ ጀምሮ ኀጢአት ሠራችሁ፤
በዚያም ጸናችሁ፤
ወይም በዚያም አቋም ወሰዳቸው

በጊብዓ የነበሩትን ክፉ አድራጊዎች፣
ጦርነት አልጨረሳቸውምን?
10በፈለግሁ ጊዜ እቀጣቸዋለሁ፤
ስለ ድርብ ኀጢአታችሁም ይቀጧቸው ዘንድ፣
በእነርሱ ላይ ይሰበሰባሉ፤
11ኤፍሬም ማበራየት እንደምትወድድ፣
እንደ ተገራች ጊደር ነው፤
በተዋበ ጫንቃዋም ላይ፣
ቀንበርን አኖራለሁ፤
ኤፍሬምን እጠምዳለሁ፤
ይሁዳ ያርሳል፤
ያዕቆብም መሬቱን ያለሰልሳል።
12ለራሳችሁ ጽድቅን ዝሩ፤
የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ዕጨዱ፤
ዕዳሪውንም መሬት ዕረሱ፤
እርሱም መጥቶ፣
ጽድቅን በላያችሁ እስኪያዘንብ ድረስ፣
እግዚአብሔርን የምትፈልጉበት ጊዜ ነውና።
13እናንተ ግን ክፋትን ዘራችሁ፤
ኀጢአትንም ዐጨዳችሁ፤
የሐሰትንም ፍሬ በላችሁ።
በራሳችሁ ጕልበት፣
በተዋጊዎቻችሁም ብዛት ታምናችኋልና፣
14ሰልማን፣ ቤት አርብኤልን በጦርነት ጊዜ እንዳፈራረሰ፣
እናቶችንም ከልጆቻቸው ጋር በምድር ላይ እንደ ፈጠፈጣቸው፣
ሽብር በሕዝብህ ላይ ይመጣል፤
ምሽጎችህም ሁሉ ይፈራርሳሉ።
15ስለዚህ ቤቴል ሆይ፤ ክፋትሽ ታላቅ ስለሆነ፣
በአንቺም ላይ እንደዚሁ ይሆናል፤
ያ ቀን ሲደርስም፣
የእስራኤል ንጉሥ ፈጽሞ ይጠፋል።”
Copyright information for AmhNASV